በትግራይ ክልል፣ የመማር ማስተማሩ ሒደት ከ50 ቀናት በፊት እንደተጀመረ ቢገለጽም፣ ወደ ትምህርት ገበታ የተመለሱት ተማሪዎች፣ ከሩብ በታች ናቸው፤ ሲል፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡
እስከ አሁን፣ ከ1ሺሕ100 በላይ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዳልጀመሩ፣ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሓላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ ገልጸዋል፡፡በሌላ በኩል፣ በመቐለ ከተማ፣ 55ሺሕ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የምገባ መርሐ ግብር መጀመሩን፣ የከተማው አስተዳደር አስታውቋል፡፡
መምህርት ዐጸደ ገብረ ጻድቕ፣ በመቐለ ከተማ፣ የአይደር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር ሲኾኑ፣ በአሁኑ ጊዜ፣ በትምህርት ቤቱ የመማሪያ ክፍሎች ውስጥ፣ ተፈናቃዮች የተጠለሉበት በመኾኑ፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በዛፍ ሥር እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በዚኽም ምክንያት፣ የመማር ማስተማር ሒደቱን አስቸጋሪ አድርጎታል፤ ብለዋል፡፡
ተማሪዎች፣ በተለይ ከወቅቱ ዝናም እና ከክረምቱ ወቅት መቃረብ ጋራ ተያይዞ፣ በዛፍ ጥላ ሥር ኾነው ለመማር ይከብዳቸዋል፤ ብለዋል ርእሰ መምህሯ፡፡በሌላ በኩል፣ በትምህርት ቤቱ የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር በመጀመሩ፣ ወደ ትምህርት ቤቱ የሚመጡ ተማሪዎች ቁጥር እንደጨመረ ተናግረዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ፣ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ፋና ጽገ፣ የተማሪዎች ምገባ መርሐ ግብር በመጀመሩ፣ ተማሪዎች እንደተደሰቱ ገልጻለች፡፡የመቐለ ከተማ አስተዳደር የማኅበራዊ ዘርፍ ሓላፊ አቶ ጌታቸው ወዳጅ፣ እስከ አሁን፣ በ26 ትምህርት ቤቶች፣ የምገባ መርሐ ግብሩ እንደተጀመረና በቅርብ ቀናት ውስጥ፣ በከተማዋ የሚገኙ ሁሉም የአንደኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች፣ በመርሐ ግብሩ እንደሚሸፍኑ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ጌታቸው እንደገለጹት፣ የምገባ መርሐ ግብሩ፣ በመንግሥት በጀት የተጀመረ ሲኾን፣ ለጋሽ ተቋማትንና ባለሀብቶችን በማስተባበር ሽፋኑን ለማስፋት ጥረት በመደረግ ላይ እንዳለ አመልክተዋል::
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ሓላፊ ዶክተር ኪሮስ ጉዑሽ በበኩላቸው፣ በክልሉ ከሚገኙ 2ሺሕ492 ትምህርት ቤቶች መካከል፣ በ1ሺሕ377ቱ፣ ከሦስት ዓመታት በላይ የመማር ማስተማር ሒደቱ ተቋርጦባቸው ከቆዩ በኋላ፣ ከ50 ቀናት በፊት ትምህርት እንደጀመሩ ገልጸዋል፡፡ በኤርትራ እና በዐማራ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ በጠቀሷቸው 552ቱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ እስከ አሁን እንዳልተጀመረባቸው ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በሚቆጣጠራቸው የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ከ500 በላይ ትምህርት ቤቶችም፣ በጦርነቱ የደረሰባቸው ውድመት ከፍተኛ በመኾኑ፣ ከኤርትራ ጋራ በሚዋሰኑ ወረዳዎች ውስጥ ያሉቱ ደግሞ፣ የጸጥታ ስጋት ያለባቸው በመኾናቸው፣ እንዲሁም የተፈናቃዮች መጠለያ በኾኑ ትምህርት ቤቶች፣ የመማር ማስተማሩ ሒደት ገና አለመጀመሩን ዘርዝረዋል፡፡
በክልሉ፣ የመማር ማስተማሩ ሒደት ስለመጀመሩ በይፋ ከተገለጸ ወደ ሁለት ወራት ገደማ ቢኾንም፣ ወደ ትምህርት ገበታ እንደሚመለሱ ከተጠበቀው የተማሪዎች ቁጥር ከሩብ በታች ናቸው፤ ብለዋል የቢሮው ሓላፊ ዶር. ጉዕሽ፡፡
ዶር. ጉዑሽ፣ የሽፋኑን ማነስ መንሥኤ ሲያስረዱም፣ ተማሪዎች አካባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸው፣ የምግብ እጥረት እንዲሁም በትምህርት አመራሮች በኩል ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ በቂ የማነሣሣት ሥራ አለመሠራቱን ጠቅሰዋል፡፡ ተማሪዎች፣ ምቹ የመማሪያ ክፍል የሌላቸው መኾኑና በቂ የትምህርት መሣርያዎች አለመኖራቸው፣ የትምህርት ሒደቱ የተሟላ እንዳይኾን አድርጎታል፤ ብለዋል፡፡
በክልሉ፣ በክረምቱ ወራትም፣ ዘመነ ትምህርቱን አራዝሞ ተማሪዎችን ለማስተማር ቢታቀድም፣ ብዙ ትምህርት ቤቶች፣ ድንኳን ተክለው እና በዛፍ ጥላ ሥር እያስተማሩ ስለሚገኙ፣ እንዲሁም የወንዞች ሙላት ለገጠር ተማሪዎች አስቸጋሪ ስለሚኾን፣ ዕቅዱ ቀሪ መደረጉን የቢሮ ሓላፊው ተናግረዋል፡፡ ስለዚኽም፣ የዘንድሮው ትምህርት፣ በቀጣዩ ሐምሌ ወር የመጀመሪያ ቀናት እንደሚያበቃና በቀጣዩ ዐዲስ ዓመት መስከረም ወር እንደሚጀምር፣ ዶር. ጉዑሽ አመልክተዋል፡፡