የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በሳምንቱ ማገባደጃ በቻይና ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል “ግልጽ እና የጎለበተ” ግኑኝነት ለመመስረት እንደሚሹ አስታወቁ። የቻይና ሰላይ ፊኛ በዩናይትድ ስቴትስ ግዛት መንሳፈፉን ተከትሎ የካቲት ላይ ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ጉብኝታቸው ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ይታወሳል ።
ትናንት አርብ አመሻሽ ላይ ወደ ቻይና ከመሄዳቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ብሊንከን በዋሽንግተን በተደረገው የጋዜጠኞች ማስገንዘቢያ ላይ እንደተናገሩት የሀገራቸው ባለስልጣናት ከቻይና አቻዎቻቸው ጋር “የምር ስጋቶች” በሆኑ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ላይ በቅንነት እንደሚነጋገሩ አስታውቀዋል ።
በጉብኝት ላይ ከነበሩት የሲንጋፖር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቪቪያን ባላክሪሽና
ጎን በመቆም መግለጫውን የሰጡት ብሊንከን ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ጋር ያላት ውድድር ወደ ፍጥጫ ወይንም ግጭት እንዳይገባ ማረጋገጥ እንደምትሻ ተናግረዋል ።
የብሊንከን ጉዞ የሁለቱን ሀገራት የሻከረ ግንኙነት ወደ ነበረበት ይመልሳል የሚለው ግምት ግን ዝቅተኛ ነው።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን አርብ ዕለት “ዩናይትድ ስቴትስ ቻይናን እንደ ‘ዋና ተቀናቃኝ’ እንዲሁም ከባድ የጂኦፖለቲካዊ ፈተና አድርጋ ትመለከታለች። ይህ በእጅጉ የተሳሳተ ትልቅ ስልታዊ ምዘና ነው።” ብለዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ጋር ያላት ፉክክር ተጠያቂነት ያለው ፉክክር ሳይሆን ኃላፊነት የጎደለው ጉልበተኝነት መሆኑን የገለጹት ዌንቢ፣ ይህም ሁለቱን አገሮች ወደ ግጭት በመገፋፋት ተከፋፈለ ዓለም እንደሚፈጥር ተናግረዋል ።
ብሊንከን ከአውሮፓዊያኑ ከ2018 ወዲህ ቤጂንግን የሚጎበኙ የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው።
በተያያዘ ዜና የውጭ ጉዳይ መ/ቤቱ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ደቡብ ኮሪያ ከቻይና ጋር “ጤናማ እና በሳል” የትብብር ግንኙነት ለመፍጠር የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ መናገራቸውን የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው ዕለት ገልጿል።
እሁድ ቻይና ይገባሉ ተብለው ሚጠበቁት ብሊንከን በሀገራቱ ሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በቻይና እና በደቡብ ኮሪያ መካከል ስላለው ግንኙነት እና ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓርክ ጂን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ዙሪያ እንደተነጋገሩ ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።