ካለፈው ሰኞ ጀምሮ በዲጂታል የክፍያ ስርዓት እየተከናወነ ያለው የነዳጅ ግብይት፣ በአዲስ አበባ ማደያዎች ከፍተኛ መጨናነቅን በመፍጠሩ ለስራ ሰዓት ብክነት እየዳረጋቸው እንደሆነ አሽከርካሪዎች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግሩ፡፡
ከዛም አልፎ ችግሩ በከተማዋ የትራንስፖርት መስረጓጎል እንደፈጠረም አሽከርካሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ በማደያዎች ነዳጅ ለመቅዳት ከአንድ ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ድረስ ወረፋ በመጠበቅ እያሳለፉ እንደሆኑ የተገለፁት እነዚሁ አስተያየት ሰጭዎች፣ በአዲሱ አሰራር ዙርያ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆን ችግሩን እንደፈጠረው አመልክተዋል፡፡
በዚህ ጉዳይ ዙርያ ለአሜሪካ ድምፅ አስተያየት የሰጠው ኢትዮ-ቴሌኮም፣ ግንዛቤው የሌላቸውን ደንበኞች ለማገዝ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልፆ፣ የግብይት መዘግየት ሁኔታው ከማደያዎች አቅም ጋር የሚያያዝ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
የነዳጅ ማደያ ሰራተኞች ደግሞ በስራ ላይ የዋለው ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ስርዓቱ እንዲህ ዓይነት ችግር እንዳይፈጥር በአንዴ ሳይሆን በሒደት መተግበር ነበረበት በማለት ተናግረዋል፡፡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በበኩሉ ደንበኞች ለዝግጅት የተሰጣቸውን ጊዜ በአግባቡ አለመጠቀማቸው፣ በማደያዎች የሚታየው መጨናነቅ እንዲፈጠር አስተዋፅኦ አድርጓል በማለት ለመንግስት ብዙሃን መገናኛ ገልፆዋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ፡፡