በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ቴኔሲ ክፍለ ግዛት ናሽቪል ከተማ በሚገኝ ክርስቲያናዊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ተኩስ የከፈተች አጥቂ ሦስት ተማሪዎችን እና ሦስት አዋቂዎችን ገድላለች። አጥቂዋን በፖሊስ በጥይት ገድሏታል።
ትናንት ሰኞ ግድያውን የፈጸመችው ቀድሞ የትምህርት ቤቱ ተማሪ ኦድሪ ሄል የተባለች የ28 ዓመት ወጣት መሆኗን የናሽቪል ከተማ ፖሊስ ያስታወቀ ሲሆን አጥቂዋ የትምህርት ቤቱን ህንጻ ካርታ በየት በኩል እንደምትገባ ጨምሮ ዕቅዷን በዝርዝር አዘጋጅታ እንደነበር አመልክቷል።
አጥቂዋ ጥቃቱን ልትፈጽም ለምን እንደፈለገች በጽሁፍ ያስቀመጠችው መግለጫዋ መገኘቱን የጠቀሰው ፖሊስ ምርመራ እያካሄደበት መሆኑን አስታውቋል።
አጥቂዋ ቢያንስ ሁለት አቶማቲክ ጠብመንጃዎች እና አንድ ሽጉጥ ታጥቃ ወደትምህርት ቤቱ ሄዳ ጥቃቱን እንደፈጸመች ፖሊስ ገልጿል።
ጥቃቱን እጅግ አሳዛኝ ሲሉ የገለጹት ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት እንዲህ ባሉ መሳሪያዎች የሚደርሱ ጥቃቶችን የሚያስቆም ህግ እንዲደነግግ ተማጽነዋል።
አጥቂዋ ሁለት ኤኬ 47 ጠብመንጃዎች እና አንድ ሽጉጥ ታጥቃ ነበር መባሉን የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ባይደን የእርሳቸውን የአቶማቲክ መሣሪያ ዕገዳ ረቂቅ ህግ ምክር ቤቱ እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል።
ቀዳማዊት ዕመቤት ጂል ባይደን በበኩላቸው ትናንት ዋሽንግተን ውስጥ በተካሄደውን የከተሞች ሊግ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር “ልጆቻችን የተሻለ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል።
እአአ ባለፈው 2022 ቴክሳስ ዩቫልዲ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ ታጣቂ ተኩስ ከፍቶ 21 ሰዎችን መግደሉ ይታወሳል።
ዝርዝሩን ከተያያዘው ዘገባ ያገኛሉ።