የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ኢራቅን ለመውረር ትዕዛዝ ከሰጡ ነገ እሁድ 20 አመት ይሞላዋል። የዛሬ 20 አመት ጦርነቱ ሲጀመር አስደንጋጭ እና አስፈሪ የቦምብ ጥቃት ዘመቻ ባግዳድን አቀጣጥሏት የነበረ ሲሆን፣ የአሜሪካ ጦር በስልጣን ላይ የነበረውን የሳዳም ሁሴን መንግስት አፍርሶ አምባገኑን መሪ ከስልጣን አውርዷል።
ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ እ.አ.አ ግንቦት 1 ቀን 2003 ዓ.ም ተልዕኳቸው መጠናቀቁን ቢያውጁም የሳዳም ባቲስት ፓርቲ አባላት እና ሌሎች አማፂያን ከአሜሪካ እና አጋር ኃይሎቿ ጋር ውጊያ በመቀጠላቸው ጦርነቱ ተራዘሟል።
ለወረራው ምክንያት የነበረው በኢራቅ አለ የተባለው የጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ ባይገኝም የኢራቅ ነዋሪዎችን እና የአሜሪካ ወታድሮችን ግን ዋጋ አስከፍሏል። የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ኦባማ አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂም ስታይንበርግን ጨምሮ በርካታ ተቺዎች አሜሪካ በኢራቅ ውስጥ ያደረገችውን ጣልቃ ገብነት “ጥበብ የጎደለው” ብለውታል።
ፕሬዝዳንት ኦባማ እ.አ.አ በ2011 የጦር ኃይላቸውን ከኢራቅ አስወጥተው የነበረ ቢሆንም ከሶስት አመት በኃላ ግን፣ በኢራቅ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ የተነሳውን እስላማዊ መንግስት ለመዋጋት በድጋሚ ገብተዋል።
ዛሬ የአሜሪካ ወታደሮች በኢራቅ የሚገኙ ሲሆን፣ ግንኙነታቸው እ.አ.አ በ2003 እንደነበረው በጠላትነት ሳይሆን በቁልፍ አጋርነት መሆኑ ነው የተገለጸው።
በኢራቅ ጦርነት ምክንያት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢራቃውያን ህይወት የጠፋ ሲሆን ከ4ሺህ በላይ የአሜሪካ ወታደሮችም ተገድለዋል።