የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ከተፈረመና ከወጣ ከ75 ዓመታት በኋላም ጥሰቱ እየተባባሰና የነበሩት መሻሻሎችም ወደ ኋላ እየተቀለበሱ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ዛሬ ተናገረዋል፡፡
በዩክሬን እየተካሄደ ያለውን ጦርነት እንዲሁም በዓለም እየጨመረ የመጣውን ድህነት፣ ረሃብና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸው አደጋዎችን በመጥቀስ የተናገሩት ዋና ጸሃፊው፣ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌው ከሁሉም አቅጣጫዎች ጥቃት እየደረሰበት ነው ብለዋል፡፡
“አንዳንድ መንግሥታት ይሸራርፉታል፣ ሌሎች ደግሞ ይደፈጥጡታል” ሲሉ ጉቴሬዝ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ም/ቤት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ምክንያት ከፍተኛው የሰብዓዊ መብት ረገጣ የታየበት እንደሆነና ከፍተኛ ሞት፣ ውድመት እንዲሁም መፈናቀል የተመዘገበበት ነው ብለዋል ጉቴሬዝ፡፡
ባለፈው ምዕተ ዓመት በሰብዓዊ መብት መከበር ላይ የታዩ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ መቀጠል ሲገባው ወደኋላ ተንሸራቷል ሲሉ ተደምጠዋል ጉቴሬዝ፡፡ በሰብዓዊ መብት ስብሰባው ላይ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ ዋናው መነጋገሪያ ይሆናል ተብሏል፡፡
ሞስኮብ ምክትል የውጪ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትሯን ሰርጌይ ርያብኮብን ሐሙስ ወደ ምክር ቤቱ እንደምትልክ ታውቋል፡፡
የስብሰባው ተሳታፊዎች የሰርጌይ ርያብኮብንን ንግግር ረግጠው እንዲወጡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥሪ በማድረግ ላይ ቢሆኑም፣ ባለፈው ዓመት በሩሲያው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰርጌይ ላቭሮቭ ላይ የተደረገው ረግጦ መውጣት ላይደገም ይችላል ሲሉ ታዛቢዎች ተናግረዋል፡፡
ዩክሬን ውስጥ እየተፈጸመ ነው የሚባለውን የጦር ወንጀል የሚያጣራው ቡድን ሥራዉን እንዲቀጥል የውሳኔ ሃሳብ እንደሚደረስ ይጠበቃል፡፡ ቡድኑ ከዚህ ቀደም በዩክሬን “በከፍተኛ ደረጃ” የጦር ወንጀል ተፈጽሟል ሲል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡