እ.አ.አ በ 2019 ዓመተ ምህረት ትውልደ ኤርትራዊውን የራፕ ሙዚቃ ኮከብ በመድረክ ስሙ ኒፕሲ ሀስል ወይም ኤርሚያስ አስገዶምን ሎስ አንጀለስ ከተማ መንገድ ዳር በጥይት የገደለው ሰው ትናንት ረቡዕ የ60 ዐመት እስራት ቅጣት ተፈረደበት፡፡
ኤሪክ ኤ ሆልደር ሎስ አንጀለስ በሚገኘው በራፐሩ የልብስ መደብር ደጃፍ ላይ በፈጸመበት ግድያ እና ወንጀሉንም የፈጸመው በጥይት በመሆኑ በሃምሳ ዐመት እስራት እንዲቀጣ የሎስ አንጀለስ ወረዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ኤች ክሌይ ጃክ ፈርደውበታል፡፡
ግለሰቡ ኒፕሲ ሀስልን ተኩሶ በገደለበት ወቅት በአቅራቢያው የነበሩ ሌሎች ሁለት ሰዎች በጥይት በማቁሰሉ ደግሞ በተጨማሪ የ10 ዐመት እስራት እንዲቀጣ ዳኛው ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡
በአንድ ወቅት የአንድ የወሮበላ ቡድን ተቀላቅሎ እንደነበረ የሚነገረው የራፕ ሙዚቃ ዘፋኙ ኒፕሲ ሀስል የተገደለው በሰላሳ ሶስት ዐመቱ ነው፡፡ በራሱ የልብስ መደብር ፊት ለፊት የተፈጸመበት ግድያ ያደገበትን የሎስ አንጀለስ አካባቢ ማህበረሰብ እና ታላቅ ዝና ያተረፈበትን ሙዚቃ ሙያውን ባልደረቦቹን እና እንዲሁም የመጣበትን ማህበረሰብ በሚጠቅሙ ሥራዎቹ የሚያደንቁትን እጅግ እንዳሳዘነ የሚታወስ ነው ፡፡
ኒፕሲ ሀስል ከህልፈቱ በኋላ እ አ አ በ2020 ዐመተ ምህረት “ራክስ ኢን ዘ ሚድል” እና “ሀየር” በሚባሉት ስየራፕ ስልቶቹ የግራሚ ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡