የቀድሞው ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን ትኩሳት ስለገጠማቸው ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው ሜድስታር ጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ገብተዋል።
የ78 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዝደንት ለምርመራ ትላንት ከሰዓት በኋላ ሆስፒታል መግባታቸውንና በጥሩ ሁኔታ መሆናቸውን እንዲሁም ለሚሰጣቸው ክብካቤ ማመስገናቸውን የክሊንተን ጽ/ቤት ምክትል ኅላፊ ኤንጀል ኡሬና ተናግረዋል።
እአአ ከ1993 እስከ 2001 የአሜሪካ ፕሬዝደንት የነበሩት ክሊንተን፣ በዚህ ዓመት በተካሄደው ምርጫ በዲሞክራቲክ ፓርቲው ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ምክትል ፕሬዝደንት ካመላ ሄሪስ ለፕሬዝደንትነት ባደረጉት ዘመቻም ቅስቀሳ በማድረግ ተሳትፈዋል።
ክሊንተን ሥልጣን ከለቀቁ ወዲህ የጤና እክል ሲደጋግማቸው ቆይቷል። እአአ በ2004 የደረት ውጋትና የትንፋሽ ማጠር ህመም ከገጠማቸው በኋላ ከፍተኛ የልብ ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸዋል። በዓመቱ፣ 2005 ሳንባቸው በከፊል እክል ገጥሞት ነበር። እአአ 2010 ደግሞ የደም መዘዋወሪያ ሥር (ኮሮናሪ አርተሪ) መተላለፊያ ቱቦ ገብቶላቸዋል።
ክሊንተን ሥጋ መመገብ አቁመው አትክልት መመገብን በማዘውተራቸው ክብደታቸውን በጣም ለመቀነስ ችለዋል።
የኮቪድ ወረርሽኝ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረበት 2021 ለስድስት ቀናት ካሊፎርኒያ የሚገኝ ሆስፒታል ገብተው የነበረ ሲሆን፣ ህመማቸው ከኮቪድ ጋራ የተገናኘ ሳይሆን በሽንት መተላለፊያ ላይ ባጋጠመ ማመርቀዝ ምክንያት ነበር።