የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ እስራኤል የሃማሱን መሪ ያህያ ሲንዋርን መግደሏ አሁንም ጋዛ ውስጥ በታጣቂው ቡድን እጅ ያሉትን ቀሪዎቹን ታጋቾች የሚያስለቅቅ ስምምነት ላይ ለመድረስ እውነተኛ እድል ማምጣቱን ተናገሩ።
ብሊንክን ይህን የተናገሩት፣ ዛሬ ረቡዕ ከቴል አቪቭ ወደ ሳኡዲ አረብያ ከመብረራቸው በፊት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው።
“እስራኤል ሃማስ ላይ በምታካሂደው ጦርነት ወታደራዊ ዓቅሙን ማዳከም ጨምሮ ብዙ ስኬት አግኝታለች” ያሉት ብሊንከን “የቀረው ታጋቾቹን ማስለቀቅ እና ጦርነቱን ማጠናቀቅ ነው” ብለዋል።
ጦርነቱ ሃማስን ከጋዛ በሚያስወጣ እና የእስራኤል ወታደሮችም እዚያ እንዳይቆዩ በሚያደርግ መንገድ መጠናቀቅ እንዳለበትም ብሊንክን አሳስበዋል።
ከጦርነቱ በኋላ ለጋዛ የሚኖረው እቅድ አስተዳደር፣ ደህንነት፣ መልሶ ግንባታ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፍልስጤማውያንን ለመርዳት ማድረግ የሚችለውን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናት ከአረብ አገሮች ጋራ የሚወያዩበት ርዕስ እንደሚሆን ብሊንከን ተናግረዋል፡፡
ብሊንከን ነገ ሐሙስ ወደካታር ይሄዱ እና አርብ በለንደን ከአረብ ሀገራት አቻዎቻቸው ጋራ እንደሚገናኙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ብሊንከን እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስተን እስራኤል ወደጋዛ የሚገባውንን የሰብአዊ ርዳታ መጠን እንድትጨምር፣ አለዚያ የአሜሪካን ወታደራዊ ርዳታ እንደምታጣ የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ ከላኩ አንድ ሳምንት በኋላ ሁኔታዎች መሻሻል ቢያሳዩም ብዙ እንደሚቀረውና ቀጣይነት እንደሚያስፈልገው የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ትላንት ረቡዕ በሰጡት መግለጫቸው ተናግረዋል፡፡
አምና የሰጡትን ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ተከትሎ እስራኤል ወዲያውኑ የሰብአዊ ርዳታ አቅርቦቱ መጠን እንዲጨምር ብታደርግም እንዳልቀጠለ ብሊንከን አውስተዋል። አዲሱ ማስጠንቀቂያ “ባዶ ማስፈራሪያ” ይሆን እንደሆን የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ” በሕጉ መሠረት ለመሥራት ቁርጠኛ ነኝ” ብለዋል፡፡
ብሊንከን ከአንድ ዓመት በፊት ከተቀሰቀሰው የእስራኤል እና የሃማስ ጦርነት ወዲህ ባደረጉት 11ኛ ጉብኘታቸው ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ እና ሌሎች ባለሥልጣናት ጋራ ትላንት ማክሰኞ ተገናኝተው ተወያይተዋል።
የሃማሱ መሪ ሲንዋርን ግድያ ተከትሎ ዩናትይትድ ስቴትስ ወደ አካባቢው ተመልሳ የተኩስ አቁም ጥረቱን እንድትገፋበት መልካም አጋጣሚ የተከፈተላት መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ኅይሎች ዛሬ ረቡዕ የሊባኖስ ደቡባዊ የወደብ ከተማ ታይር ላይ የአየር ጥቃት አካሂደዋል፡፡ ጥቃቱን ያደረሱት ነዋሪዎች ከተማዋን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ከሰጡ ከሰዓታት በኋላ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ሌሊቱን ቤይሩት ውስጥ ያሉ ከሄዝቦላህ ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካባቢዎች ደብድበናል ስትል እስራኤል አስታውቃለች፡፡
ዛሬ ረቡዕ ቤይሩትን የጎበኙት የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አናሌና ቤርቦክ ለሊባኖሱ ጦርነት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡