ባለፈው መስከረም መጨረሻ ሐማስ በእስራኤል ላይ የከፈተውን ጥቃት አቀናብረዋል በሚል የሚከሰሱት በጋዛ ሠርጥ የሐማስ መሪ የነበሩት የህያ ሲንዋር የድርጅቱ የፖለቲካ ሃላፊ እና በጋዛ ወታደራዊ መሪ ሆነው ተመርጠዋል።
የህያ ሲንዋር በጋዛ የሚካሄደውን ጦርነት በድርድር ይፈታሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ተንታኞች በመግለፅ ላይ ቢሆኑም፣ የሐማስ ቃል አቀባይ ግን የህያ ሲንዋር ድርድሩን ይቀጥላሉ ብለዋል።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ምኒስትር አንተኒ ብሊንከን አሁን በጋዛ ለ10 ወራት የቆየውን ግጭት በተኩስ አቁም መቋጨት የየህያ ሲንዋር ፈንታ ነው ብለዋል። ምክንያቱም አሉ ብሊንከን “የህያ ሲንዋር ዋና ውሳኔ ሰጪ ነበር፣ አሁንም ነው” ብለዋል።
የህያ ሲንዋር ባለፈው ሳምንት ኢራን ውስጥ የተገደሉትን ኢስማኤል ሃኒየህን የተኩ ሲሆን፣ በአንፃራዊነት ለዘብተኛ ተደርገው የሚቆጠሩት ሃኒየህ በሕይወት በነበሩበትም ወቅት የህያ ሲንዋር ወሳኝ መሆናቸው ተነግሯል።
የእስራኤል እና የአሜሪካ የደህንነት ባለሥልጣናት ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደገለጹት፣ የየህያ ሲንዋር ዓላማ በጋዛ የሚካሄደው ጦርነት እንዲቀጥል በማድረግ እስራኤል በዓለም አቀፍ መድርክ ክብሯ እንዲቀንስ ማድረግና ከዋና አጋሯ አሜሪካ ጋርም ያላትን ግንኙነት ማበላሸት ነው።
የህያ ሲንዋር እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ምኒስትር ቤንጃሚን ኔተንያሁ ለየግላቸው ፖለቲካ ምክንያት ሲሉ የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ እንደማይደርሱ ተንታኞች በመናገር ላይ ናቸው።