“20 ቀናት በሜሪየፖል” በተሰኘው እና ሩሲያ በዩክሬን የወደብ ከተማ ላይ ያደረገችውን ከበባ አስመልክቶ በሰራው ዘጋቢ ፊልም የመጀመሪያውን ኦስካር ሽልማት ለሀገሩ ያስገኘው ዩክሬናዊ የፊልም ዳይሬክተር ሚስቲስላቭ ቸርኖቭ፣ ኦስካር ከሚሸለም ይልቅ በሀገሩ ላይ ጦርነት ባይታወጅ ይመርጥ እንደነበር ተናግሯል።
ለአሶስዬትድ ፕሬስ የዜና ወኪል የቪዲዮ ዘጋቢ የሆነው ቸርኖቭ፣ ቪልሙን የቀረፀው እ.አ.አ በ2022 ዩክሬን ሩሲያን በወረረችባቸው የመጀመሪያ ቀናት፣ ከባልደረቦቹ ጋር ከሜሪየፖል ከተማ መውጣት ባልቻሉባቸው ቀናት ነው። ፊልሙ እሁድ እለት በተካሄደው የኦስካር ሽልማት ላይ በምርጥ ዘጋቢ ፊልም ዘርፍ አሸናፊ ሆኗል።
ቸርኖቭ “በዩክሬን ታሪክ ይህ የመጀመሪያው የኦስካር ሽልማት በመሆኑ ትልቅ ክብር ይሰማኛል” ሲል በታላቅ ቆሞ በታላቅ ጭብጨባ ለተቀበለው ታዳሚ ተናግሯል።
“ምናልባት ግን እዚህ መድረክ ላይ፣ ይህንን ፊልም በፍፁም ባልሰራ ምኞቴ ነው ብሎ በመናገር የመጀመሪያ ዳይሬክተር ሳልሆን አልቀርም” ያለው ቸርኖቭ፣ ይህን ሽልማት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት በማታደርስበት እና ከተሞችን በማትቆጣጠርበት ሁኔታ ብቀይር ደስ ይለኝ ነበር፣ ነገር ግን ታሪክን መቀየር፣ ያለፈን ነገር መቀየር አልችልም” ሲል ስሜቱን ገልጿል።
እ.አ.አ በ2022 ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ፣ ሩሲያ በተቆጣጠረቻት ሜሪየፖል፣ ከተማዋን ለቀው መውጣት ያልቻሉ ሰላማዊ ዜጎች ሟቾችን በመንገድ ዳር እንዲቀብሩ በመገደዳቸው፣ በወቅቱ የነበረው አስከፊ ሁኔታ ምሳሌ ነበረች።
በከበባው ወቅት ቢያንስ 8 ሺህ ሰዎች በጦርነቱ ወይ ከጦርነቱ ጋር ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች የሞቱ ሲሆን፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ለሁለት ዓመታት የሚጠጋ ጊዜ ከተካሄዱ ውጊያዎች ትልቁ መሆኑን ሂዩማን ራይትስ ወች የተባለው ተቋም በየካቲት ወር አስታውቆ ነበር።
ሽልማቱን ተከትሎ ቸርኮቭ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ “ይህ የአስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እና ጥቃት እየደረሰባቸው እና እየተገደሉ ያሉ ሲቪሊያኖችን የመርዳት ጉዳይ ነው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።